በጄኔራል ታደሰ ብሩ ዋና ግቢ የስድስት ቀን የስልጠና መርሃ ግብር ያዘጋጀው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፕሪነርሽፕ አና ቢዝነስ ኢንኩቤሽን ሴንተር ዳይሬክቶሬት ሲሆን
በስልጠናው የተሳተፉት ደግሞ ከተለያዩ ኮሌጆችና ትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ ከ60 በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ናቸው፡፡ ስልጠናውም የተሰጠው ከኢትዮጲያ ሥራ ፈጠራ አመራር ኢንስቲትዩት በመጡ አሰልጣኞች ነው፡፡
ስልጠናው በዋናነት ያተኮረው በስራ ፈጠራ መሰረታዊ የንግድ ንድፈ ሃሳብ ማፍለቅ፤ የስኬት መንገዶች፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት በስራ ዘርፍ የስኬት መልካም ተሞክሮዎች፤ ከስልጠና በኋላ ከሰልጣኞች ምን ይጠበቃልና ወዘተ በመሳሰሉት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ነው፡፡ ሰልጣኞቹም በሁለት ምድብ ተከፍለው የሰለጠኑ ሲሆን ስልጠናውም ተግባር ተኮር ስራዎች ላይ ያተኮረና ተግባራዊ የአመለካከትና የባህሪ ለውጥ የሚያመጣ ስልጠና ነው፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ፕሮግራም ላይ በመገኘት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገናነው ጎፌ እንደተናገሩት እንዲህ አይነቱ ስልጠና በሁሉም በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ በቡድንም ሆነ በግል በምንኖረው ህይወት ውስጥ ስኬታማ ስራ እንድንሰራና የእያንዳንዳችንን የኑሮ ደረጃ ድሮ ከነበርንበት ወደ ፊት የሚያራምድና ከግልም አልፎ ለአገር እድገት እጅግ የጎላ አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ከስልጠናው የተገኘውን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም በአገርና በዓለም አቀፍ ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ተግባር በመቀየር ብሎም ለሌሎች ማህበረሰብ አርአያና ምሳሌ በመሆን የበኩላችንን ድርሻ ከተወጣን የምንፈልገውን ሁሉ በቅርብ ግዜ ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡
በስተመጨረሻም አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በተሰጣቸው ስልጠና የተደሰቱ መሆኑን ገልጸው፤ስለ ስራ ፈጠራ ብቁ የሚያደርጉ መሰረታዊ የስራ ፈጠራ ክህሎቶችን ወደ ተግባር በመቀየር ስኬታማ ስራ እንደሚሰሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በስልጠናው የሚጠበቅባቸውን አስፈላጊ ሁኔታዎችን በብቃትና በንቃት ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡