ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን 232 በድህረ ምረቃ፣ 107 በመደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ በጤና ሳይንስ፣ ተማሪዎችን በአጠቃላይ 339
ተማሪዎችንና በ 'HDP' ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 28 መምህራን በሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ በደማቅ ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የሰላሌ ዩንቨርስቲ ሴኔት አባላት፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች አቶ ገበየሁ ሀብቴ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ፣ የፊቼ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ክፍሉ ከበደ፣አባ ገዳዎች ፣ሀዳ ስንቄዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣መምህራንና የተመራቂ ወላጆች ተገኝተዋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገናነው ጎፌ በምረቃት ፕሮግራም መርሀ ግብሩ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ውድ ተመራቂ ተማሪዎቻችን ከበርካታ ዓመታት ልፋትና ትጋት በኋላ ላስመዘገባችሁት ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የሚቀጥለው ጊዜ ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ የምትሸጋገሩበት ጊዜ ነውና፣በሃይማኖትና በጎሣ ሳትለዩ ከሙስና በፀዳ መንገድ ሀገራችሁና ማህበረሰባችሁን በቅንነትና በታማኝነት እንድታገለግሉ እንዲሁም በሄዳችሁበት ሁሉ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር በመሆን እንድትሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ በማለት ተናግረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አቶ ገበየሁ ሀብቴ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት የስራ መመሪያ መልዕክት መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መፍትሄው ትምህርት መሆኑን በማመን እውቀትና ክህሎት ያለውን ዜጋ ለማፈርት ለትምህርት ትኩረት ሰጥቶ ስፊ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡እናንተም በዛሬው ዕለት የተመረቃችሁ ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባፈራችሁ ዕውቀትና ክህሎት የአገራችሁን አደራ ወደ ጎን ሳትተዉ የበለጸገችና ያደገች ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋትና በቅንነት መስራት ይኖርባችሁዋል በማለት ለተመራቂ ተማሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በስተመጨረሻም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ለተመራቂ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡